Fana: At a Speed of Life!

ወልድያ ከተማን መልሶ ለማልማትና ለማቋቋም ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል – ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወልድያ ከተማን መልሶ ለማልማትና ለማቋቋም ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ገለጸ ፡፡

የወልድያ ከተማ ባደረገለት ጥሪ መሰረት አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በከተማዋ ተገኝቶ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡

ረጅም ጊዜ ባደረገው የአዋጭነት ጥናትም ወልድያ ከተማ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ናት ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ተናግሯል፡፡

በጥናቱ መሰረትም በከተማዋ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መወሰኑን ነው የገለጸው፡፡

በከፍተኛ ወጪና ጥራት የተገነባውን የሼህ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲ ስታዲየን የቀሩትን በማሟላትና የደረሰበትን ጉዳት በማስተካከል ወደ ስራ በማስገባት ስፖርተኞችን ማፍራት ይገባልም ብሏል።

አትሌቱ ከተማዋ ለቱሪዝምና የንግድ እንቅስቃሴ አመቺ በመሆኗ በወልድያ ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ ትልቅ ዕድል መሆኑን አውስቷል፡፡

የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ÷በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥም በከተማዋ ያሉ ጸጋዎችን በመለየት የባለሃብቶችን ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

5 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ወደ ስራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በአንድነት ናሁሰናይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.