Fana: At a Speed of Life!

የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ የተጀመሩ ምርትን የማሳደግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ የተጀመሩ ምርትን የማሳደግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢኮኖሚ ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥቅሉ በአሃዝም በመስተጋብርም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ከዓለም ጋር ያለው መስተጋብር እየሰፋ ሲሄድ ዓለም ላይ የሚደርሰው ተጽኦኖ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሀገር ላይ ተጽኦኖ አለው ብለዋል፡፡

በዚህም ዓለም ላይ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ ችግሮች ዓለም አቀፍ ባንኮች ሲጎዱ፣ የብድር አለመክፈል፣ የዋጋ ግሽበትና ሌሎች በቀጥታ ኢትዮጵያን ተጽዕኖ ውስጥ ይከቷታልም ነው ያሉት፡፡

የዋጋ ግሽበት መንስዔዎች በርካታ ቢሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት እና የኮቪድ-19 ስርጭት መሆናቸውን አይ ኤም ኤፍን ዋቢ በማድረግ አንስተዋል።

በዚህም 184 ሀገራት በዋጋ ግሽበት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ከእነዚህም ውስጥ 110 ሀገራት ከ10 በመቶ በላይ የዋጋ ግሽበታቸው ማደጉንም ነው የድርጅቱን ሪፖርት ጠቅሰው ያብራሩት፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በታች ዜጎች ያሏቸው 37 ሀገራት በዋጋ ግሽበቱ ህልውናቸውን አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ችግር እንዳጋጠማቸው ጠቅሰዋል፡፡

በቁጥር ማደግ ብቻ ሳይሆን ምርታማ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ያደጉ ሀገራት የኢኮኖሚ ቀውሱን ለመፍታት ከሚያደርጉት ጥረት መማር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

ይህን እንደዓለም የመጣውን ችግር ለማምለጥም ሁሉም ኢትዮጵያዊ መዘጋጀት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የጀመርናቸውን መነቃቃቶች በተሟላ መንገድ መስራት ብቻ መፍትሄ እንደሆነም ነው ያመላከቱት፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እድገቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱን አንስተውም ፥ ይህም ከዓለም ጋር ያለንን መስተጋብር መሰረት በማድረግ ችግሩ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳም ገልጸዋል፡፡

ከሠሃራ በታች ያሉ ሀገራትም ከ3 ነጥብ 8 በመቶ ያላነሰ እድገት ያመጣሉ ሲል አይ ኤም ኤፍ በሪፖርቱ እንዳስታወቀም ነው ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያም 5 ነጥብ 7 እድገት እንደሚኖር ድርጅቱ ያለውን ግምት ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያን እድገት ከሚፈታተኑ ችግሮች ዋነኛው የብድር ዕዳ መንግስት መውረሱ ነው ብለዋል።

የክፍያው ጊዜ የደረሰውን የኢትዮጵያ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ዕዳ መከፈሉን ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ንረት ሌላኛው ችግር መሆኑን በማንሳት፥ ይህም የውስጥ ችግርና ከውጭ በምናስገበው ምርት የመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የመሰረተ ልማት ክፍተት ነው።

አራተኛውና ዋነኛው ብለው ካነሷቸው የኢኮኖሚ ችግሮች አንዱ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ በዚህም ምርትን በማብዛት ያለውን እጥረትና ሽሚያ መቀነስ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው የዋጋ ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳና እየጎዳ እንዳለ በጽኑ እንገነዘባለንም ብለዋል፡፡

መንግስት ምርትን ማሳደግ እንደሆነ እንደመፍትሄ መውሰዱን እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.