Fana: At a Speed of Life!

የጌትስ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመግታት በማካሄድ ላይ ያለችውን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ የ200 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ የኮቪድ – 19 ወይም የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ሥርጭት ለመከላከል እና ለመግታት በማካሄድ ላይ ያለችውን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ የ200 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
 
ፋውንዴሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ሌሎች የቴክኒክ እና መሰል ድጋፎችን የሚያካትተው እገዛ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል እየተወሰዱ ያሉ የመመርመር፣ ወረርሽኙን የመለየት እና የማከም እንዲሁም የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በተለይም ደግሞ ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ነው።
 
የጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ወረርሽኙን ለመከላከል እና በጉዳዩ ላይ ማኅበረሰባዊ ንቃትን ለመፍጠር እየተወሰዱ ያሉ ፈጣን የቅድመ ጥንቃቄ፣ የማስተባበር እና የቁጥጥር እርምጃዎችን አድንቋል።
 
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ባልተጠበቀ ወቅት የተከሰተውን ችግር ለመከላከል በተለይም በአነስተኛ ኢኮኖሚያዊ አቅም ላይ የሚገኙ የማኅበረሰባችን አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ በትኩረት ርብርብ እያደረገ መሆኑም ነው ያመለከተው።
 
ይህም ድጋፍ የመንግሥትን ወረርሽኙን የመከላከል እና የመቆጣጠር ጥረት ያግዛል ብለው እንደሚያምኑም በኢትዮጵያ የጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ኃላፊ አቶ ሀዲስ ታደሰ ገልፀዋል።
 
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት፥ ፋውንዴሽኑ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስታውቅዋል።
 
እንዲሁም የገንዘብ ድጋፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ የሚቀንስ መሆኑንም ነው የገለፁት።
 
ኢንጂነር ታከለ አክለውም፥ “የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የህዝባችን ትክክለኛ አጋር መሆናቸውን በአስፈላጊው ወቅት ስላሳዩን ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.