Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤክስፖርት ምርት እድገት ላይ እንዲያተኩር አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቋሚ ኮሚቴው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤክስፖርት ምርትን በማሳደግ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳሰበ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ የተመለከተ ሲሆን ÷ በሂደቱም ከፓርኩ አመራሮች፣ ሰራተኞችና ከባለኃብት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በ102 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ካሉት 19 ሼዶች 16ቱ በባለኃብት መያዛቸውንና ስራ መጀመራቸውን፣ 8 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት እስካሁን ብቻ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የመስክ ምልከታ ቡድኑ በጥንካሬ ተመልክቶታል ተብሏል።

የመስክ ምልከታው ቡድን መሪ ዘውዱ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ÷ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ የተሻለና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም ባለኃብት ትኩረቱን በኤክስፖርት ንግዱና የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካት ላይ እንዲያደርግ ጥረት መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

ከ16 ሼዶች አብዛኛዎቹ በውጭ ባለኃብቶች መያዛቸውን እንደተረዱ ጠቅሰውም ÷ ፓርኩ የሀገር ውስጥ ባለኃብቶችን ለማበረታታት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበትም አመላክተዋል።

የአንዳንድ ሰራተኞች ደመወዝ ያለውን የኑሮ ውድነት ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ባለኃብቱን በመሳብ ሂደት ውስጥ ዝቅተኛ የሰው ጉልበት የሚለው አመለካከት ጭምር መስተካከል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ተቋሙ ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠርና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑ የመብራት መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመሳሰሉ የባለኃብት ጥያቄዎችን ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡና አፈጻጸሙንም እንደሚከታተሉ አመላክተዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.