Fana: At a Speed of Life!

ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ የግብይትና የእርድ ስርዓቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከትንሳዔ በዓል ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ የግብይትና የእርድ ስርዓቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ።

የጤና እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ የኮሮናቫይረስን መከላከል ላይ መደረግ ባላለበት ጥንቃቄ ዙሪያ ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የግብይት ስርዓቶች ጥንቃቄ በተሞላበት እና ርቀትን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የእርድ እንስሳትን በተመለከተ እስካሁን ባለው መረጃ ቫይረሱ ከሰው ወደ እንስሳት ሊተላለፍ ስለሚችል በግብይት ወቅት የሚደረጉ ልማዳዊ እንስሳትን የመነካካት ተግባር ቢቀርም መልካም ነው ብለዋል።

በእርድ ወቅትም በተቻለ መጠን ባለቤት ቢያርድ መልካም ነው ያሉት ዶክተር ሊያ፥ ካልተቻለ ግን በቄራዎች ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል።

በእርድ በሚከናውን ባለሙያ የሚደረግ ከሆነ ግን ደህንነትና ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ ሊከናወን ይገባል፤ በዚህም እርድ ለሚያከናውነው ባለሙያ የእጅ ጓንት እና የአፍ መሸፈኛ ማዘጋጀት የግድ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እርዱ በጋራ የሚከናወን ወይም ቅርጫ ከሆነ ደግሞ ከተቻለ ባለቤቱ አሊያም ደግሞ ጥቂት ሰዎች በተገኙበት ብቻ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መከናወን አለበት ያሉት ሲሆን፥ ይህንነም በእያንዳንዱ ሂደት እጅን በአግባቡ በሳሙና መታጠብ እንዲሁም የእጅ ጓንት እና የአፍ መሸፈኛ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ስጋ ከመብላት ጋር ተያይዞም ቫይረሱ ስጋን በመብላት ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል የሚለው የተሳሳተ እና እስካሁን ማረጋገጫ ያልተገኘለት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ጥሬ ስጋን መብላትን አንመክርም ያሉት ሚኒስትሯ፥ ስጋው የግድ መብሰል አለበት፤ የበሰለ የእንስሳት ተዋዕፆ ከጤናም አንፃር አስፈላጊውን አቅም ስለሚሰጠን መመገብ ጠቃሚ ነውም ብለዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ በበዓል ግብይት ውቅት መጨናነቅና የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ከግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘም አስተማማኝ አቅም ስላለ ህብረተሰቡ ምንም ስጋት ሳይገባው በተረጋጋ መልኩ ጥንቃቄ በተሞላበትና አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ ግብይት እንዲፈፅም ጠይቋል።

በባሃሩ ይድነቃቸው

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.