Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በአምስት ዞኖች የኮሌራ ክትባት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የኮሌራ በሽታ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ከ76 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ክትባት መስጠት መጀመሩን የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በባሌ፣ በጉጂ፣ ምዕራብ አርሲ፣ በምስራቅ ባሌ እና በምስራቅ ቦረና ዞኖች በሽታው መከሰቱን ገልፀዋል።

በሽታው መከሰቱ የተረጋገጠው ቅኝት በማድረግና በቤተ ሙከራ ምርምራ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ክትባት መስጠት እና ንፅህናን መጠበቅ ጨምሮ ሌሎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች በስፋት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በበሽታው ለተያዙ ግለሰቦች መድኃኒትና ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሽታው አዋሳኝ በሆኑ የኬንያ ግዛቶች መከሰቱን ተከትሎ በሞያሌና አጎራባች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ በመደረግ ላይ መሆኑንም የቢሮው ኃላፊ አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ንጽሕና በመጠበቅና የህክምና ባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ ገቢራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት በመግታት ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.