Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ድሬዳዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአስተዳደሩን አጠቃላይ የስራ ሂደት ያብራሩ ሲሆን÷ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የፀጥታ፣ የመሰረተ ልማት፣ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ የወጣቶች ስፖርት ማዕከላት፣ የድሬደዋ ምድር ባቡር እና ኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመርን ጨምሮ ለከተማዋ በስጋትነት የሚጠቀሰው የጎርፍ ጉዳይ ተነስቷል።

ከንቲባው በሌሎች ቦታዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ከተማዋ ውስጥ ያለውን ሰላም ለማወክ ሲሞክሩ እንደነበር አስታውሰው ከወጣቶች እና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በቅርበት እና በቅንጅት በመስራት ከተማዋን ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ እንደተቻለ ገልጸዋል።

የህዝብ ጥያቄዎችን በማዳመጥ እና አንገብጋቢ ጉዳዮችን በመለየት ያላለቁ እና ለረጅም ጊዜ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ወጣቶች አልባሌ ቦታዎች እንዳይውሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደተሰሩ፣ ድሬዳዋ ያላትን ተፈጥሯዊ ሀብት መጠቀም እንድትችልም በፀሀይ ብርሀን ሀይል ማመንጨት የሚያስችላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በከተማው ውስጥ አምስት የውሀ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን÷ ከ300 ቤቶች በላይ እንደተገነቡ እና በአመት 10 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ጎርፍን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማህበረሰቡ ከህግ ውጭ ቤቶችን ባለመገንባት አስተዳደሩ እየሰራ ያለውን ስራ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

በትዕግስት አስማማው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.