Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቋርጥ ውሳኔ አሳለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቋርጥ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሃላፊነቱን አልተወጣም ሲሉ ወቅሰዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ድርጅቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ አስተዳደር ተከትሏል በማለት እና ቫይረሱ በቻይና ከተቀሰቀሰ በኋላ ድርጅቱ ለስርጭቱ ሽፋን ሰጥቷል በማለት ይከሳሉ።

ለዚህም ድርጅቱ ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ነው ፕሬዚዳንቱ የሚናገሩት።

ሆኖም ፕሬዚዳንቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በያዙበት መንገድ ዙሪያ በሀገራቸው ዜጎች እና ፖለቲከኞች ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኮሮና ቫይረስን ፖለቲካዊ ማድረግ አይገባም ሲሉ በድርጅታቸው ላይ የሚቀርበውን ወቀሳ አጣጥለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ለዓለም ጤና ድርጅት የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጥ አሁን ሰዓቱ አይደለም ብለዋል።

አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋነኛዋ ድጋፍ አድራጊ ሀገር ስትሆን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የተቋሙን በጀት 15 በመቶ ወይም 400 ሚሊየን ዶላር ሸፍናለች።

ምንጭ፡- ቢቢሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.