Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የአንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት አነሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡
 
በጉባኤውም የፍትሕ ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው የአንድ ምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ያነሳው፡፡
 
ያለመከሰሰ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤት አባልም የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ጫላ ዋታ ናቸው፡፡
 
ዶ/ር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የመንግስት ግዢ ስርዓትን ሳይከተሉ የተለያዩ የተጋነኑ ግዢዎችን ፈጽመዋል በሚል በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ነው፡፡
 
በስማቸው በተመዘገበ የባንክ አካውንት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በመግባቱና በባለቤታቸው ስም የመኖሪያ ህንጻ ተመዝግቦ በመገኘቱም በዋነኛነት ተጠርጣሪ የሆኑባቸው ነጥቦች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
 
የምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዶ/ር ጫላ የተጠረጠሩበት ወንጀል ለመፈጸማቸው በቂ አመላካች ነገር መገኘቱን ጠቁሟል።
 
ምክር ቤቱ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የቀረበውን ሀሳብ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.