Fana: At a Speed of Life!

መንግስታት የአንድ ወገን ማዕቀብን እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ውሳኔ ፀደቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (ዩ ኤን ኤች አር ሲ) መንግስታት የአንድ ወገን ማዕቀብ እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ውሳኔ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ሰኞ ዕለት ሁሉም ሀገራት የዓለም አቀፍ ህግን እና የሀገራትን ሰላማዊ ግንኙነት የሚገዙ መርሆዎችን የማያሟሉ የአንድ ወገን የማስገደድ እርምጃዎችን እንዲያቆሙ የሚያሳስብ ውሳኔ አሳልፏል።

ውሳኔው በ33 ድጋፍ፣ በ13 ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ መፅደቁን ነው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ ያመላከተው።

የአንድ ወገን አስገዳጅ እርምጃዎች በሰብአዊ መብቶች ተጠቃሚነት ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅእኖ ያገናዘቡ እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ዘጋቢ ጠይቃለች።

እንዲሁም በቀጣይ ለምክር ቤቱ የሚቀርበው ሪፖርት ተጠያቂነትን ለማበረታታት በሚያስፈልጉ ሀብቶች እና የካሳ ስርዓቶች ላይ እንዲያተኩር ውሳኔው ይጠይቃል።

በተጨማሪም የውሳኔ ሃሳቡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት የአንድ ወገን የማስገደድ እርምጃ በመልማት መብት እና በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ አስመልክቶ በየሁለት አመቱ የፓናል ውይይት እንዲያዘጋጅ ጠይቋል።

ይህ ውይይትም የፊታችን መስከረም ወር 54ኛው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.