Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች በልማት እና ከወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች ለተነሱ ዜጎች መኖሪያ ቤት አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልማት እና ከወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት አስረከቡ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ዛሬ ከፍል ውሃ አካባቢ፣ ከጉለሌ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች በልማት እና ከወንዝ ዳርቻ ለተነሱ ነዋሪዎች 200 ምትክ መኖሪያ ቤት አስረክበናል ብለዋል፡፡

እንዲሁም 525 ኮንዶሚኒየም ቤት፣ ለግል ይዞታ ባለቤቶች 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ካሳ እና 5 ነጥብ 6 ሄክታር ምትክ መሬት ማስረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

የወንዞቻችን ዳርቻ አካባቢዎች በደረቅና ፍሳሽ እንዲሁም ከፋብሪካ በሚለቀቁ ቆሻሻዎች በመበከላቸው በሰው ልጅ ላይ የጤና ችግር የሚያስከትሉ፣ በዝናብ ወቅት በሰውና በንብረት ላይ አደጋ የሚያደርሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ይህን በመቅረፍ የነዋሪውን ህይወት ከአደጋ ለመታደግ በተገባው ቃል መሰረት እና ከተማዋን ንጹህ ፣ ውብና አረንጓዴ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ እና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ከእንጦጦ እስከ ወዳጅነት ፓርክ 5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ መጀመሩን አመላክተዋል።

“በተግባር የነዋሪዎቻችንን ችግር ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ ሁሉም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆንባት ከተማ መገንባታችንን እንቀጥላለን” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.