Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ቦታው ድረስ በመገኘት አበረታተዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር በመሆን የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ቦታው ድረስ በመገኘት አበረታተዋል።

በኤካ ኮተቤ ሆስፒተሰል የተገኙት መሪዎቹ በተቋሙ እያገለገሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እና ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአረጋውያንን ቤት ማደስ መርሀግብርን ያስጀመሩበት እማሆይ አዱኛ መኖሪያ ቤትና የአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት በመገኘትም ለፉሲካ በዓል የሚሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል።

በተጨማሪም አፍንጮ በር አካባቢ ሚገኝ የህፃናት ማሳደጊያ ተገኝተው የፋሲካ በዓል ስጦታ ማበርከታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጉብኝቱን አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃም፥ “ያለንበት ጊዜ፣ ከመቼውም ይልቅ አካላዊ ርቀታችንን እየጠበቅን ማኅበራዊ ትሥሥራችንን ማጠናከርን የሚጠይቅ ነው፤ ወደ ልባችን ጠልቀን ርኅራሄን ማፍለቅ እና በልግስና ለሌሎች መትረፍ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

“የከፋ ችግር ለገጠማቸው የድጋፍ እጃችንን የምንዘረጋበት እና የጋራ መከራችንን በአንድነት የምንጋፈጥበት ጊዜ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

“የፊታችን እሑድ የፋሲካ በዓል የሚከበርበት እንደ መሆኑ፣ እኔም የተቀበልሁትን ብዙ በረከት እጅግ ለሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰባችን አካላት አካፍያለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “በክበበ ፀሐይ የሚኖሩት ሕፃናት ብርታት፣ በመንደሬ የሚገኙት የጎረቤት አዛውንት ሴቶች ብልሐት፣ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚገኙ የሕክምና ባለሞያዎች እና ታካሚዎች ጽናት፣ የሰው ልጅን የመንፈስ አይበገሬነት አሳይተውኛል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ እርስ በእርሱ እንዲረዳዳ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ህብረተሰቡ በየአካባቢው ድጋፍ የሚያደርግበት 1 ሺህ 200 የምግብ ባንኮች አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.