Fana: At a Speed of Life!

ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለነዳጅ 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ለነዳጅ 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ክፍያ ስርአትን ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ በቢሾፍቱ ምክክር እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፥ የነዳጅ ግብይት በፖሊሲ ታግዞ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ጥሩ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፖሊሲ የተደገፈ አሰራር ከመጀመሩ ከሰኔ 2014 ዓ.ም በፊት የነዳጅ ግብይት ስርዓቱ ለከፍተኛ ችግርና ለዕዳ ጭምር የተዳረገ ነበር ብለዋል።

በነዳጅ አቅርቦት ስርዓት ላይ ያሉ የመሰረተ ልማት እና የአሰራር ክፍተቶች ነዳጅን ለኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ እያጋለጡ የቆዩ ችግሮች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡

ይህንን ክፍተት ለማስቀረትም በኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ዘመናዊ ስርአት ውስጥ አጋር አካላት የሆኑ መንግስታዊ ተቋማት የአጋዥነት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱ በፖሊሲ ተደግፎ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሂደቱ ከነበረበት ችግር እንዲወጣ ከማስቻል ባለፈ ግልጽነት እንዲኖረው ማስቻሉን ተናግረዋል።

በመንግሥት እየተደረገ የሚገኘው የነዳጅ ድጎማ ስርዓትም ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዳ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱ በፖሊሲ ተደግፎ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መደጎሙንም ጠቅስዋል።

ከዚህ ውስጥ 8 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ድጎማን አነስተኛ እና መካከለኛ ህዝብ ማመላላሻ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በዚህም የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ግቡን እየመታ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በብርሃን ደሳለኝ እና በሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.