Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ ለኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
 
ባለሥልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ÷ ኢሳት ቴሌቪዥን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፉ /ያልተረጋገጡ፣ የህዝቦችን መተማመንና አንድነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ እያቀረበ መሆኑን አንስቷል፡፡
 
በዚህምተቋሙ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1185/2012 እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በመጣስ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጸው፡፡
 
ለአብነትም ጣቢያው የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም “የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ሸገር ከተማ የዜጎችን ቤት በማፍረስ ግፍ መፈጸሙን ድምጻዊ መብሬ መንግስቴ ተናገረ፡፡ ድምጻዊው ዜጎች ላይ የተፈጸመው በደል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ገልጿል”… የሚል ዜና ማቅረቡን አንስቷል፡፡
 
በዚህም በዘገባው የተጠቀሱ አካላት ሃሳብና አስተያየት ሳይካተት ድምዳሜ ላይ የደረሰ በመረጃ ያልተደገፈና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ አስተላልፏል ሲል ባለስልጣኑ አብራርቷል፡፡
 
መጋቢት 6 ቀን 2015ዓ.ም “የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ከተማ የሚገቡ ዜጎችን አስመልክተው ያደረጉት ንግግር ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭና የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚጥስ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ” የሚል መረጃ ያቀረበ ሲሆን÷ በዘገባው “የጫካ ፕሮጀክት አንድ ሚሊየን የሚጠጋ በጣም አቅመ ደካሞች የሚባሉ ዜጎች አፈናቅሏል፡፡ የቤት ፈረሳውን የሚመራውን ግብረ ኃይል ቤቶቹን ከማፍረስ ባሻገር የንብረት ዘረፋ ውስጥ ተሰማርተዋል፤ የሚገድሉ፣ የሚዘርፉ እና የሚደበድቡ ሰዎች ናቸው እያስተዳደሩን ያለው” የሚሉ በሰነድ/ማስረጃ ያልተረጋገጡና የተቋማትን መልካም ስም የሚያጠፉ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ማሰራጨቱንም አንስቷል፡፡
 
ቴሌቪዥን ጣቢያው ከላይ የተጠቀሰውን እና ሌሎች ከጋዜጠኝት ስነምግባርና መርህ ጋር የሚጣረሱ፣ ማህበራዊና ተቋማዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ክፍተት ያለባቸውን ዘገባዎች ማሰራጨቱ ተመላክቷል፡፡
 
የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/1(ሀ) እና (ለ) ፕሮግራሞች ወይም ዜናዎችን የተለያዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ አጠቃላይ ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ሚዛናዊ እና ከአድሎ የጸዱ አድርጎ ማቅረብ፣ የሚሰራጩ ፕሮግራም ወይም ዜና ይዘትና ምንጭን እውነተኛና ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሰራጩ ሪፖርቱ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሚል የተቀመጡ ህጎችን አለማክበሩም ተጠቁሟል፡፡
 
ስለሆነም ኢሳት ቴሌቪዥን ሚዛናዊነት የጎደላቸው ሀሰተኛ ዘገባዎችን በማሰራጨት በሕዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.