Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ፣ ጣልያን እና ሶማሊያ ያላቸውን የሶስትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ጣልያን እና ሶማሊያ ያላቸውን የሶስትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ እና ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ውይይታቸው በዋናነት የሀገራቱን የሶስትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
 
ውይይቱን የተከታተሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም እንዳሉት÷ መሪዎቹ ከሶስትዮሸ በተጨማሪ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር ረገድ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ መግለጻቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
 
በተጨማሪም በተለይ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካካል ያለው የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በተለይ በመንገድ መሰረተ ልማት ለመተሳሳር በሚያደርጉት ጥረት ላይ ጣልያን አጋር እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ መግለጻቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ይህ ተግባራዊ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚኖሩም ነው የተመላከተው፡፡
 
በሌላ መልኩ የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያና ሶማሊያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በሚሰማሩበት ጉዳይ ላይ መሪዎቹ መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡
 
የጣልያን ኩባንያዎች በተለይ በኢትዮጵያ በግብርና በቱሪዝምና ታዳሽ ሃይል ዘርፍ እንዲሰማሩ የጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ ተናግረዋል፡፡
 
በሶማሊያ ያለው አንጻራዊ ሰላም ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑ በሶስትዮሽ ውይይት መድረኩ ላይ መነሳቱን ቢልለኔ ስዩም ጠቁመዋል፡፡
 
የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ ሁኔታዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡
 
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ይበልጥ እየተነቃቃ እንደሆነ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.