Fana: At a Speed of Life!

በአሰላ ሪፈራልና የማስተማሪያ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሰላ ሪፈራልና የማስተማሪያ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተጀመረ።

በአርሲ ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው ሆስፒታል የተጀመረው ምርመራ በቀን 72
ናሙናዎችን የመርመር አቅም አለው ነው።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ነሞ አምቦ በሆስፒታሉ ከዚህ በፊት በነበረ ትሮፒካል ኸልዝ ቤተ ሙከራ ምርመራው መጀመሩንና የመመርመር አቅሙን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ለመመርመሪያ ማዕከሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሟላታቸውንና የጤና ባለሙያዎችም ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

የጤና ሳይንሶች ኮሌጅ ዲን መርጋ ባዩ በበኩላቸው የመመርመሪያ ማዕከሉ ስራ መጀመር
የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚከናወነውን ስራ ያግዛል ብለዋል።

መመርመሪያውም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፈቃድ ማግኘቱን ነው ያስታወቁት።

ከመመርመሪያው በተጨማሪ የማከሚያና ለይቶ ማቆያ ስፍራዎች የተዘጋጁ ሲሆን፥ የበቆጂ ሆስፒታልን ለኮሮና ህክምና መስጫነት የማደራጀት ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው ተብሏል።

በክልሉ የኮሮና ምርመራ ማዕከላትን ለማስፋት በመሰራት ላይ ነው ያሉት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በቀጣይ በጅማና ወለጋ ዩኒቨርስቲዎች ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

በክልሉ በአዳማና ሀሮማያ ዩኒቨርስቲዎች ከዚህ ቀደም የኮሮና ምርመራ መጀመሩ ይታወሳል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.