Fana: At a Speed of Life!

በዓሉን ስናከብር ደም በመለገስና ያለንን በማካፈል እንዲሆን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የትንሳኤ በዓልን ስናከብር በድንገተኛ የህክምና ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቻችን የሚሆን ደም በመለገስና ካለን በማካፈል መሆን እንዳለበት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

ወይዘሮ አዳነች በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘትም ደም ለግሰዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደም መለገስን ጨምሮ አለኝ የሚለውን ማንኛውንም ነገር ለወገኖቹ በማካፈል በዓሉን እንዲያሳልፍም ጥሪ አቅርበዋል።

“ልግስና እና ደግነት” ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበት አብሮ የቆየና
የዳበረ እሴት መሆኑንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ “ነገር ግን በዚህ ወቅት አስቸኳይ ደም የሚሹ ወገኖች መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።

በመሆኑም ይህን በመረዳት ደም የመለገሱ መልካም ጅማሮ ሊቀዛቀዝ አይገባም ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ፤ ለዚህ በጎ ተግባር አርአያ ለመሆንም በዛሬው እለት በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት ደማቸውን ለግሰዋል።

የብሔራዊ የደም ባንክ በቅርቡ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ታያይዞ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቁጥር እንደቀነሰበት አስታውቋል።

ሆኖም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የደም ባንኮች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው ደም ለጋሾችችን እንዲያስተናግዱ ዝግጁ ሆነዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.