Fana: At a Speed of Life!

 ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 444ኛው ዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥርን በዓል ሲያከብር በመተሳሰብ እና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለ1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በመላው ዓለም ለምትገኙ ሙስሊሞች በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ብለዋል፡፡

ዒድ አል ፈጥር ዓመቱን ጠብቆ በሂጅራ አቆጣጠር የተከበረውን የረመዷን ወርን ተከትሎ ሸዋል ወር አንድ ሲል፣ የሸዋል ጨረቃ ስትወጣ የሚከበር ተወዳጅና ሙስሊሞች በደስታ፣ በመተሳሰብ እና በአብሮነት ስሜት የሚያሳልፉት ልዩ ውበትና ድምቀት ያለው በዓል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ወርሃ ረመዳንን በተለያዩ ኢባዳዎችና ካላቸው ነገር ላይ ለጎረቤትና ለተቸገሩት በማካፈል፣ በመቀራረብና በልዩ ልዩ የመልካም ሥራዎች መስተጋብር እያንዳንዷን ቀን ሙስሊሞች መልካም ሥራቸውን በሙሉ አላህ እንዲቀበላቸው፣ ቀጣይ ዓመት ረመዷንንም በሰላምና በጤና እንዲያደርሳቸው ዱአ በማድረግ ዒድ አል ፈጥርን ያከብራሉም ነው ያሉት፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ÷በረመዳን ፆም ሰለምና ፍቅር የሚሰፍንበት፣ መረዳዳትና መተጋገዝ የሚታይበት፣ ነፍስና ስጋ ለቅድስና የሚገዛበት ወር ነው ሲሉ ለዒድ-አልፈጥር በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በረመዳን ወር የሙስሊሙ ማህበረሰብ የፅድቅ ሥራ የሚሰራበት የአላህ (ሱወ) የጀነት በሮች የሚከፈቱበት፣ ሰይጣን የሚታሰርበት ቅዱስ ወር ነውም ብለዋል፡፡

በረመዳን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከኃጢያት የሚሸሽበት፣ ከአሉባልታና ከሐሜት ራሱን የሚገታበት፣  ተንኮልንና ንፉግነትን ተጠይፈው ለሌሎች በደግነት እጁን የሚዘረጋበት ቅዱስ ወር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ÷ ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በተከተለ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ በጾም ወራት ያሳየውን መተሳሰብ በበዓሉ ወቅትም ሆነ በሌሎቹም ጊዜያት መድገም እንዳለበትም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሐረሪ ክልል መንግስት ለስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 444ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም በተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር እንዲያከብር የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ በተለይም በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመደጋገፍንና መረዳዳት እሴት በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር ያስፈልጋልም ብሏል።

በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ወርን በጾም፣ በዱዓ፣ በሶደቃ፣ በመተጋገዝ፣ በመረዳዳትና በሌሎች ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ማሳለፉን አስታውሰዋል፡፡

የእስልምና እምነት ተከታዮች እርስ በእርስና ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድም እህቶቹ ጋር ለዘመናት የገነባውን መልካም መስተጋብር የበለጠ በማጠናከር በሀገሪቱ ልማትና ሰላም ግንባታ ላይ ሚናውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥርን በዓል ሲያከብር በመተዛዘን፣ በመተጋገዝና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ለዒድ አልፈጥር በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በተለይም በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመደጋገፍና መረዳዳት እሴት በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.