Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶቻቸውን ከሱዳን እያስወጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶቻቸውን ከሱዳን ማስወጣት ጀምረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን÷ በሱዳን ካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው በዛሬው ዕለት ሀገሪቷን ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዲፕሎማቶቹ የአሜሪካ ጦር ባካሄደው የተሳካ ኦፕሬሽን ነው ከሱዳን ካርቱም በሰላም መውጣት የቻሉት፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ድፕሎማቶችን ለማስወጣት ለተደረገው የተሳካ ስራ ለኢትዮጵያ፣ጅቡቲ እና ሳዑዲ ዓረቢያ መንግስታት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ በሱዳን የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ ማረጋገጣቸውንም ቢ ቢ ሲ ዘግቧል፡

በተመሳሳይ 150 የሚሆኑ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብጽ፣ ካናዳ፣ ሕንድ፣ ኩዌት፣ ፓኪስታን እና የቱኒዚያ ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች በባህር ከሱዳን ሳዑዲ ዓረቢያ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

ፈረንሳይ ፣ ቻይና፣ ብሪታንያ ፣ ስፔን እና ሌሎች ሀገራትም በሱዳን ካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶቻቸውን ለማስወጣት ስራ መጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡

በሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በሚመሩት የሱዳን ጦር እና ምክትላቸው መሃመድ ሀምዳን ደጋሎ በሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተፈጠረው ግጭት ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል፡፡

በግጭቱም እስካሁን 425 በላይ ንጹሃን ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡

የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ግጭቱን በማርገብ ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.