Fana: At a Speed of Life!

የሸዋል ዒድ በሐረር መከበር ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ሕዝብ መገለጫ የሆነው የሸዋል ዒድ በዓል በሐረር ከተማ መከበር ጀምሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ÷ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ ቀጄላ በበዓሉ አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሐረሪዎች ባህላቸውን እና ቅርሳቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ይደግፋል ብለዋል።

አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መገለጫ የሆኑት ባህል፣ ቋንቋ እና ዕሴቶች ውበታችን ስለመሆናቸው የሸዋል ዒድ ክብረ በዓል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

የሐረሪ ሕዝቦች ባህልና ቅርስ ጥበቃ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት እውቅና መሠጠቱንም ጠቁመዋል፡፡

የሐረር ሥነ ጽሑፍ ቡድን፣ የሐረር ብሔራዊ ሙዚየም እና የሸሪፍ የግል ሙዚየም በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የሸዋል ዒድ በዓልን ጠብቆ በተካሔደው “የጀጎል አዋርድ” ሽልማት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

የ2015 የጀጎል አዋርድ ብቸኛ አሸናፊው አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ (የክብር ዶ/ር) ናቸው፡፡

አሸናፊው ግለሰብ ለ34 ዓመታት ቤታቸውን ወደ ሙዚየምነት በመቀየር ከ30 ሺህ በላይ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ጠብቆ በማስቀመጥ ለትውልድ ያሻገሩ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የአምስት አጎራባች ክልሎች የባህል ቡድኖች የተገኙበት 1ሺህ 444ኛው የሸዋል ዒድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ተከፍቷል።

የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽኑን አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ ኦርዲን በድሪ ናቸው መርቀው የከፈቱት፡፡

በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር በሸዋል ወር ሥድስቱ የሱና ጾም ከተጾመ በኋላ ሐረሪዎች የሚያከብሩት የሸዋል ዒድ በዓል ባህላዊ ዕሴታቸውን የሚገልጹበትን ጭምር መሆኑ ይታወቃል።

በዓሉ በክልሉ የመቻቻል፣ የአብሮነት እና የሰላም ዕሴትን እንዲሁም በተለይ የቱሪዝም ዘርፉን ከማጎልበት አንፃር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሸዋል ዒድ በዓል አከባበርን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሣንይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመራኦል ከድር እና ያስሚን ሰዒድ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.