Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ የሚሆን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልሎች ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ሥራ የሚሆን 1 ቢሊየን 675 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የአማራ እና የአፋር ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የሦስቱንም ክልሎች ህዝብ በጋራ ልማት ለመካስ እንሠራለን ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ 30 ትራክተር እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ለትግራይ ክልል ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው ÷ አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመገንባትም ቃል ገብተዋል።

የክልሉ ህዝብ ካለው ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አንስተው ÷ በዚህም በአጠቃላይ 1 ቢሊየን ብር የሚሆን የልማት ተሳትፎ እናደርጋለን ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ የትግራይ ክልልን መልሶ ማቋቋም ስራ ለማጠናከር አንድ ጤና ጣቢያ እና አንድ ትምህርት ቤት መገንባትን ጨምሮ በመጀመሪያው ዙር እስከ 500 ሚሊየን ብር የሚደርስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ÷ አጋርነታችንን ለማሳየት ሁለት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት በጋራ ርብርብ መስራትን የሚጠይቅ በመሆኑ 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገናል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁኻር ÷ ሰላማችንን ለማፅናት የሁሉም ትብብር ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ከቁሳቁስ ባሻገር 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ÷ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከትግራይ ህዝብ ጎን መቆሙን ለማረጋገጥ 15 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ÷ ያለፈውን ተምረንበት ወደፊት መልካም ነገሮችን ለመገንባት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም ክልሉ አዲስ ቢሆንም የትግራይ ህዝብን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ÷ ተባብረን ከሰራን በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት መካስ እንችላለን ብለዋል።

የደቡብ ህዝቦች 1 ሺህ 500 ኩንታል የዘር ግብዓት እና የእርሻ መሳሪያዎችን ጨምሮ 20 ሚሊየን ብር የዓይነት እንዲሁም 30 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ የክልሉ ህዝብ በትግራይ ክልል የሚኖሩ ወገኖቹን ለማገዝ 20 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው ÷ በተጨማሪም የ10 ሚሊየን ብር የዓይነት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኑስራ አብደላ በተመሳሳይ ክልሉ በመጀመሪያ ዙር 10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ ÷ 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.