Fana: At a Speed of Life!

“ከፍታ የወጣቶች ፌስቲቫል” በአዲስ አበባ ሚኒሊየም አዳራሽ መከናወን ጀምሯል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣትነት ለለውጥ፣ ለሥራ ፈጠራና ለሀገር ግንባታ ሙሉ ትኩረት ሰጥተው የሚጥሩበት ዕድሜ ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናገሩ።

“ከፍታ የወጣቶች ፌስቲቫል” በዩ ኤሴ. አይ.ዲ ፣ በማሪፍ ኢትዮጵያ እና በሌሎች አጋር አካላት ትብብር በዛሬው ዕለት በሚኒሊየም አዳራሽ መከናወን ጀምሯል።

በፌስቲቫሉ ላይ ለወጣቶች መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ እንኳን ወደ አፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በሰላም መጣችሁ ያሉ ሲሆን ወጣትነት ለነገ ስኬት መልካም ስብዕናን በመላበስ በንቃት የሚጥሩበት የሽግግር ዕድሜ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥር በመጠቀም ለማልማት መንግስት ለወጣቶች ጉዳይ ትኩረት በማድረግ ምቹ ፖሊሲዎችን የአሰራር መዋቅሮችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ወጣቶች ለሰላም ትኩረት በመስጠት በምክንያታዊነት በማመን እራሳቸውን ከጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያነት ሊከላከሉ ይገባልም ነው ያሉት።

የወጣቶች ፌስቲቫሉ ወጣቶችን ለመልካም ጉዳዮች ለማነቃቃት የእርስ በርስ ግንኙነት ለማሳደግ አዳዲስ መንገዶችን ለማመላከት በመከናወን ላይ ይገኛል።

በፌስቲቫሉ ላይ ከመላው ኢትዮጵያ ከተሞች የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ወጣቶች ከስኬታማ የንግድና የትምህርት ዓለም ግለሰቦች ጋር ለማስተሳሰር የልምድ ልውውጥ ስልጠናዎች እንደሚኖሩ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.