Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በመጪው ሰኞ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን /ሜይ-ዴይ/ በመጪው ሰኞ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

ቀኑ በኢትዮጵያ ለ48ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ134ኛ ጊዜ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን /ኢሠማኮ/ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ቀኑን በማስመልከት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሣሁን ፎሎ እንዳሉት ÷ሠራተኛው ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት እንዲሁም ምርትና ምርታማነቱ ማደግ እንዲችል ሰላም ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ ሰላማዊ ንግግሮች መጀመራቸው መልካም መሆኑን ጠቁመው ÷ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር በነፃነት የመደራጀትና የመደራደር መብት በሕገ-መንግሥቱም ጭምር የተደነገገ ቢሆንም አንዳንድ አሠሪዎች ግን ይህ እንዳይሆን ጫናዎችን በማሳደራቸው መፍትሔ ሊበጅለት ይገባልም ሲሉም ነው የተናገሩት።

በዓሉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ገልጸዋል።

የዓለም የሠራተኞች ቀን/ሜይ-ዴይ/ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1890 ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር ቆይቷል።

የዘንድሮው በዓልም “ለሠራተኞች መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሔ” በሚል መሪ ሀሳብ ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከበር የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.