Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው በጃክ ማ የተበረከቱ የህክምና ቁሳቁሶች እያሰራጨ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በመጀመሪያ ዙር በጃክ ማ የተበረከቱትን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መመርመሪያ መሳሪያዎችና የህክምና መገልገያዎችን እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ።

በጃክ ማ ሁለተኛ ዙር የተሰጠው ድጋፍም ለስርጭት ዝግጁ ሆኗል ተብሏል።

በመጀመሪያ ዙር በእርዳታ የተሰጠውን የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪቶችና የህክምና መገልገያዎች እየተሰራጩ መሆኑን የኤጀንሲው መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች የመጋዘንና የክምችት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው መኮንን ገልጸዋል።

ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚያስችሉ 20 ሺህ 89 የመመርመሪያ ኪቶች፣ 47 ሺህ 950 N95 የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ 1 ሺህ 100 መከላከያ ሙሉ ፕላስቲክ ልብሶች፣ 52 ሺህ የፊት መሸፈኛ ጭምብል እና 1 ሺህ የፊት መከላከያ ፕላስቲክ በመሰራጨት ላይ ናቸው።

የህክምና ግብአቶቹ ስርጭት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥያቄ መሰረት እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል።

በጃክ ማ በሁለተኛ ዙር የተሰጠው ድጋፍም በኤጀንሲው መጋዘኖች ገብተው ለስርጭት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በቻይና መንግስት በእርዳታ የተሰጠውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ የሙቀት መጠን መለኪያ (ኢንፍራሬድ ቴርሞሜትር) ጨምሮ ሌሎች የህክምና ግብአቶችን ማሰራጨቱን አውስተዋል።

በጃክማ ፋውንዴሽን ለተደረገው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍም አቶ እንዳልካቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.