Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል በእርሻ ዘርፍ መሬት ወስደው ያላለሙ የ285 ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰረዘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት ወስደው ያላለሙ 285 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው መሰረዙን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ከተሰረዘ 285 ባለሀብቶች መካከል 36 የሚደርሱት ከልማት ባንክ ብድር የወሰዱ መሆናቸውም የጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመግለጫቸው፥ በክልሉ ከ700 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የእርሻ ኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሰሞኑን ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የኢንቨስትመንት እርሻ መሬት ተቀብለው ያላለሙ 285 ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ በመሰረዝ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቀዋል።

ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ባለሀብቶች መሬት ተረክበው ወደ ስራ ያልገቡ፣ ስራ ጀምረው ያቆሙ፣ የመሬት መጠቀሚያ ግብር ያልከፈሉና ከልማት ባንክ ብድር ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ፈቃድ የተሰረዘባቸው ባለሀብቶች ከአቦቦ 45፣ ከጋምቤላ ወረዳ 56፣ ከዲማ 75፣ ከኢታንግ ልዩ ወረዳ 105፣ ከላሬ 3 እና ጎደሬ ወረዳ አንድ ባለሀብት መሆናቸውን አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.