Fana: At a Speed of Life!

እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በቀጣዩ ግንቦት ወርም ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በቀጣዩ የግንቦት ወርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በአንዳድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ የሚያስገኙ የሜቲዎሮሎጂ ክስተቶች ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የኢንስቲትዮቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና የቅደመ ማስጠንቀቅያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ( ዶ/ር) እንደገለጹት÷እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።

ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ አየር ሁኔታ ክስተቶች በሀገሪቱ ደቡባዊ አጋማሽ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በእነዚሁ አካባቢዎች ከአነስተኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በተለይ ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጀም፣ ዋግህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ አፋር ዞኖች ከባድ ዝናብ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ፣ ሰሜንና ምስራቅ ሸዋን ጨምሮ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረሪ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ቦረና እና ጉጂ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሀገሪቱ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች መካከል የደቡብ አጋማሽ ሶማሌ ክልል፣ ሁለቱ ጉጂ ዞኖች፣ ሁለቱ ባሌ ዞኖች፣ ቦረና ዞን፣ ደቡብ ክልል፣ ሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተጠቃሽ ናቸው።

በነዚሁ አካቦቢዎች በተለይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ በመሆኑ ከጎርፍና መሰል አደጋዎች ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሱማሌ ክልል፣ የደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ጉጂ፣ ቦረና፣ ከደቡብ ክልል የጂንካ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ሌሎች አካባቢዎችም የበልግ ዝናብ በጥሩ ሁኔታ የሚያገኙ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.