Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከፊንላንድ አቻቸው ፔካ ሃቪስቶ ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ ጋር በሁለትዮሽ፣ ክልለዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

አቶ ገዱ በነበራቸው የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው ሁለቱ አገራት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገች ያለውን አጠቃላይ እንቅስቀሴ በመግለጽ፤ ሁለቱ አገሮች የኮሮናን ስርጭት ለመግታት በትብብር መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል።

አቶ ገዱ አክለውም፥ ፊንላንድ ለአረንጓዴ ልማት እያደረገች ያለውን ድጋፍ በመመስገን ይህው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨመሪም የኢትየጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበትን ወቅታዊ ደረጃ እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብዕ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ያደረጉትን ውይይት በተመለከተም አቶ ገዱ ገለጻ አድርገዋል።

የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ስለተደረገላቸው ገለጻ በማመስገን ፈንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኘነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ፊንላንድ የኮሮና ቫይረስን ለመከለከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት እንደምትደገፍ እና ተሞክሯዋን ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሶስቱ አገሮች ውይይት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው እና በዚህ በኩል የፊንላንድ እገዛ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗንም ፔካ ሀቪስቶ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1951 ዓ.ም ነው፤ ፊንላንድ በ1951 ዓም አዲስ አበባ ላይ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ስዊድን ስቶክሆልም በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ፊንላንድን ሸፍና ትሰራለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.