Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ-19 የዓለም ስጋትነት ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮቪድ-19 የዓለም ጤና ስጋትነት ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አደረገ።

ሁኔታውን አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ወረርሽኙን ለመግታት ብዙ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ያወሳው መግለጫው÷ ቫይረሱ ዓለም አቀፍ የጤና አደጋ መሆኑን ካወጀ ከሦስት ዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ ስጋትነቱ ማብቃቱን በይፋ አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ ባለሥልጣናት እንደገለፁት ቫይረሱ ያስከትል የነበረው የሞት መጠን በፈረንጆቹ ጥር 2021 በሳምንት ከ 100 ሺህ በላይ ሰዎች ከነበረበት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 24 2023 ወደ 3 ሺህ 500 ቀንሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንደተናገሩት በወረርሽኙ በዓለም በትንሹ ሰባት ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጋ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ይህም ከይፋዊው ግምት ሶስት እጥፍ የሚጠጋ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ነገር ግን ቫይረሱ አሁንም ትልቅ ስጋት ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ውሳኔው ለተወሰኑ ጊዜያት በጥንቃቄ የታሰበበት እና መረጃን በጥንቃቄ በመመርመር የተወሰነ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ አብቅቷል ማለት አደጋው አብቅቷል ማለት እንዳልሆነ እና ሁኔታው ከተቀየረ የአደጋ ጊዜ አዋጁ ወደነበረበት ሊመለስ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ ጥር 2020 ኮቪድ-19ን የዓለም የጤና ስጋት አድርጎ ማወጁ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.