Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት ከወከሉ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያን በእስያ እና ፓሲፊክ ሀገራት ከወከሉ አምባሳደሮች እና ቆንስላ ጄኔራሎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ዙሪያ ለአምባሳደሮቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳሮቹ በተወከሉበት ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ መረጃ ኖሯቸው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በሚጠብቁበት ዙሪያ ኤምባሲዎች እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ገዱ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይስን ለመከላከል እያደረገች ላለው እንቅስቃሴ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ስላለው ድጋፍ በማመስገን፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም አምባሳደሮቹ ከሚኖሩበት ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሀገራት ኮሮናን ለመከላከል እየወሰዱ ያለውን እርምጃ እና ተሞክሮ በመቀመር በሪፖርት የማሳወቁ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ የእስያ ፓሲፊክ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዳዊት ይርጋ እና በእስያ ፓሲፊክ ሀገራት የተወከሉ ሁሉም አምባሳደሮች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.