Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ብጥብጥና ሁከት የሚቀሰቅሱ እና የሚሳተፉ አካት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚዝያ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልል እና ሀገር አፍራሽ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው ብጥብጥና ሁከት የሚቀሰቅሱ እንዲሁም የሚሳተፉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አሳሰበ፡፡

የክልሉ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን ነው ብሏል፡፡

ጥቂት ኃይሎች በቅንነት ሀገራቸውን ባገለገሉ ሃቀኞች ስም በመጠቀም የግል ጥቅማቸው እንዳይቋረጥ አደረጃጀት የፈጠሩበትን መሰረታዊ ዓላማ በመዘንጋትና ፖለቲካዊ መልክ በመስጠት፣ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ባልሆነበት ሁኔታ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ ትንኮሳ በማድረግ ክልላችንና ሀገሪቱን ወደ ትርምስ በመውሰድ በውጭና በውስጥ የተደራጁ ኃይሎች መጠቀሚያ ለመሆን ተንቀሳቅሰዋል ብሏል መግለጫው፡፡

የመግለጫው ሙሉቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን ነው!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዜጎችን ሰላም፣ ህልውና፣ የኑሮ መሻሻል እና ብሔራዊ አንድነትን ማፅናት የሚያስችሉ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የፖሊሲ ጉዳዮችን በመፈፀምና በማስፈጸም ውጤታማ ክንውኖችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከገጠሙን ፈተናዎች ጋር ፅኑዓን ሁነን እስከ መስዋዕትነት ድረስ በመታገል የለውጡ ምዕራፍ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሕዝባችን በሰላም፣ በልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ እየተደረገም ይገኛል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት መነሻ በማድረግ የፌዴራል መንግሥቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ከታጠቁ ኀይሎች ጋር በገባበት ጦርነት ሕዝባችን የብዙ ጉዳቶች ሰለባ ሁኖ አልፏል። እንደ ሀገር የተፈፀመብንን ወረራ ለመቀልበስ መላው የክልላችን ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተባብሮ ጉዳቱን ማስቆምና መቀልበስ ተችሏል፡፡

የክልላችን መንግሥት የድኅረ- ጦርነት እቅድ አውጥቶ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም፤ ጉዳት ለደረሰባቸው በቂ እንክብካቤ ማድረግ፣ የፈረሱ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን መልሶ ማደራጀት፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መጠገን ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕዝባችን ላይ ፀንቶ የነበረው የጦርነት ስነ ልቡና ወደ ቀደመው የሰላምና ልማት ስነ ልቡና ለመመለስ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እየተሠሩም ይገኛል፡፡

በድኅረ ጦርነት የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውጭ በፈቃደኝነት ተሰባስበው በጎ አስተዋጽኦ ላደረጉ ቡድኖች አስፈላጊውን እውቅና እና የጀግና የክብር ሽልማት በማበርከት የትውልድ ተምሳሌቶች ተደርገው እንዲዘከሩ አድርጓል፡፡

በጦርነት ጊዜ ሁሉም ተዋጊና ተጠራጣሪ እንዲሁም የተጠቂነትና የመወረር ስነ ልቡና የነበረበትን ሁኔታ ቀይሮ የተገኘውን የሰላም አየር በመጠቀም ወደ መልሶ መቋቋም፣ ልማትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። በክልሉ ውስጥ እየተስፋፋ የነበረውን የጦርነት አድማስ ለመቀልበስ የተንቀሳቀሰውን ሃይልም ወደ ሰላማዊ ሕይዎቱ ለመመለስ እና አይበገሬ የልማት አርበኛ አድርጎ ለመጠቀም መጠነ ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረት በፈቃደኝነት ሕዝባቸውን ከጥቃት ለመከላከል አደረጃጀት ፈጥረውና በግንባር ተሰማርተው አኩሪ ገድል ለፈጸሙት ወገኖቻችንም ይኸው የሰላም አማራጭ ተዘርግቶ ቀጣዩን ዘመን በሕዝባቸው ዘንድ ተከብረው ወቅቱ የሚጠይቀው አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት ብዙ ጥረቶችና ውይይቶች አድርጓል፡፡

ሁኖም ግን በእነዚህ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ሃይሎች በቅንነት ሀገራቸውን ባገለገሉ ሃቀኞች ስም በመጠቀም የግል ጥቅማቸው እንዳይቋረጥ አደረጃጀት የፈጠሩበትን መሰረታዊ ዓላማ በመዘንጋትና ፖለቲካዊ መልክ በመስጠት፣ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ባልሆነበት ሁኔታ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ ትንኮሳ በማድረግ ክልላችንና ሃገሪቱን ወደ ትርምስ በመውሰድ በውጭና በውስጥ የተደራጁ ሃይሎች መጠቀሚያ ለመሆን ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ነገር ግን ዛሬም ቢሆን በዚህ ተግባራቸው ምክንያት የመንግሥት ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይታጠፉ የሰው ሕይወት ያጠፉ፤ የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር ለማፍረስ ትንኮሳ ያደረጉ፤ ዘረፋና የለየለት ውንብድና ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት ሕዝብ አስታግሱልን በማለት ጥያቄ ያቀረበባቸው እና በከፍተኛ ሆደ ሰፊነት የቀረበውን የሰላም አማራጭ ገፍተው መንግሥትን ደካማ ለማድረግና ለመገዳደር የሞከሩ ቡድኖች ላይ መንግስት በተመረጠ ሁኔታ ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ይገኛል፡፡

የሕግ ማስከበር እርምጃው በገለጽናቸው ምክንያቶች ችግር ባለባቸው በጣም ውስን የክልላችን አካባቢዎች የሚደረግ እንጂ ሁሉንም የክልላችን አካባቢዎች የሚመለከት አለመሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጽንፈኛ የሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ “አንቂ” ነኝ ባይ እንደሚለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥም አለመሆናችን መታወቅ አለበት፡፡ እንዲያውም ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፤ ሠርቶ እንዳይበላ ለማድረግ የሚሞክሩትንና ከሰላማዊ አማራጮች ጋር የተፋቱትን ቡድኖች እንድናስታግስለት አበክሮ ሲጠይቅ የቆየ መሆኑን ራሱ ሕዝባችን የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡

በሌላ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘው የሕግ ማስከበር ሥራ የአማራን ሕዝብ ትጥቅ ማስፈታት አለመሆኑን ደጋግመን ለሕዝባችን አሳውቀናል፡፡ እየተከናወነ የሚገኘው የሕግ ማስከበር የክልላችንን ሕዝብ ወደ ዘላቂ ሰላም በማስገባት የሕዝባችን የትግል ዓላማ አልፋና ኦሜጋ የሆነውን ሰላም፣ ፍትሐዊ ልማትና ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ የሕግ ማስከበር ሥራ የትኛውም በክልላችን የሚኖር ሰላማዊ ዜጋ ሠርቶ የሚለወጥበት፤ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት እንዲሁም ለአንድ ዓላማ ሕዝባዊ አንድነት ፈጥረን ቀጣይ የትግል መስመሮችን አብረን በመጓዝ ለበለጠ ድል የምንበቃበትን መንገድ የሚተልም መሆኑን መላው ሕዝባችን ሊገነዘበው ይገባል፡፡

የክልላችን መንግሥት ዛሬም ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን እደሆነ ያምናል፡፡ ስለሆነም ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች ጥምር የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የአገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በፅናት የተዋደቁ ሰማእታትን ጀግንነት ከንቱ በሚያደርግ መንገድ የተሰለፋችሁ እንዲሁም የሕዝባችን ጥቅሞች ላይ በመቆም የተሳሳተ ዓላማ ውስጥ የገባችሁ ፅንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች ከእኩይ ድርጊታችሁ ተቆጥባችሁ መንግሥት ያስቀመጣቸው የሰላም አማራጮች ተጠቃሚዎች እንድትሆኑ ዛሬም ደግመን ደጋግመን እናሳስባለን፡፡

በአንዳንድ ጽንፈኛ የማኅበራዊ ሚዳያ ተጠቃሚዎች የሚደረገው ከመንግሥት የሕግ ማስከበር ዓላማ ውጭ የሆነ፤ የሕዝብን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች የሚያሳጣ እና ሕዝባችን በየጊዜው እንታገልባቸው ዘንድ የሰጠን መሰረታዊ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ስልቶች የማይደግፍ እንዲሁም ሃገርን ወደ ትርምስ የሚመራ የሁከትና የብጥብጥ ቅስቀሳ ሁሉ ፈጽሞ ስህተት እና ክልላችንና እና ሕዝባችንን ዋጋ የሚያስከፍል እንዲሁም ለተራዘመ ጊዜ የሚያጎሳቁል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም በዚህ ክልልና ሀገር አፍራሽ ተግባር ውስጥ ተሠማርታችሁ ብጥብጥና ሁከት የምትቀሰቅሱና የምትሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁሉ ከድርጊታችሁ ልትቆጠቡ ይገባል፡፡

“ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን ነው!!”

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.