Fana: At a Speed of Life!

በቋራ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የቋራ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ዋና ሳጅን ዳምጠው ሞላ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ነብስ ገበያ ቁጥር አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተለያዩ ጥይቶችን ይዞ ሲንቀሳቀስ ነው።

ግለሰቡ የሰሌዳ ቁጥር በሌለው ሞተር ሳይክል 1 ሺህ 142 የክላሽኮቭና 500 የብሬን ጥይቶች እንዲሁም 38 የክላሽ ካዝናዎች ይዞ መገኘቱን ገልፀዋል።

ወረዳው ከሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በወጣው አዋጅ መሰረት የፀጥታ አካላት ቁጥጥር በሚያደርጉበት ወቅት ግለሰቡ መያዙንም ተናግረዋል።

ከድንበር ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያም ሆነ የሰዎችን ዝውውር ለመግታት የተጠናከረ የድንበር ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ወንጀለኞችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.