Fana: At a Speed of Life!

የደም መርጋት መንስኤ እና ምልክቶቹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድ ጤናማ ሰው ሰውነት ውስጥ ከ5 እስከ 7 ሊትር ደም እንዳለ ይታመናል፡፡

ደም ያለምንም መስተጓጎል በደም ቱቦ በኩል የሚዘዋወር ሲሆን÷ ለሰከንዶች እንቅስቃሴው ቢቆም ወደ ጠጣርነት በመቀየር ይረጋል፡፡

ለዚህም በምክንያትነት የሚነሳው ደም 45 በመቶ ጠጣር፤ 55 በመቶ ውኃ ስለሆነ ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

የደም መርጋት ሲባልም÷ በሰውነት ውስጥ በሚገኝ በአንድ(ከዚያ በላይ በሆነ) ደም መላሽ (ቬን) ውስጥ የደም መጓጎል (መርጋት) መከሰት ማለት ነው፡፡

በአብዛኛው በእግር አካባቢ እንደሚከሰትም ይገለጻል፡፡

ለዚህም ምክንያቶቹ÷ የተለያየ የጤና ችግር፣ ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ አለማድረግ (ለረጅም ጊዜ መቆም፣ መቀመጥ) እንደሆኑ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡

የእግር ማበጥ፣ የእግር ህመም፣ የእግር መቅላት ወይም መጥቆር፣ የእግር መሞቅ ከምልክቶቹ መካከል ሲጠቀሱ÷ ምልክት ላያሳይ የሚችልበት ጊዜ እንዳለም ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

የረጋ ደም በደም ስር ተጉዞ ወደ ሳንባ በመሄድ ቱቦ ዘግቶ በሳምባ ውስጥ አየርና ፈሳሽ እንዲጠራቀም በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የጤና ዕክል ሊያስከትል ስለሚችል÷ አንድ ሰው ከላይ የተገለጹት ምልክቶች ሲኖረው ወደ ሕክምና ተቋም እንዲሄድ ይመከራል፡፡

በቤተሰብ ደም መርጋት ካለ፣ ለብዙ ጊዜ የአልጋ ቁራኛ የሆነና ፓራላይዝድ የሆነ ሰው፣ ቀዶ ጥገና የተሰራለት ከቀዶ ጥገና በሗላ፣ ሲጋራ አጫሾች፣ የካንሰር ታማሚ፣ የልብ ችግር ያለባቸው፣ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆሙ እና የሚቀመጡ ሰዎች ለደም መርጋት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡

ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል÷ ለረጅም ጊዜ አለመቀመጥ (አለመተኛት፣ አለመቆም)፣ እግርን አለማጣመር፣ ክብደት መቀነስ፣ ሲጋራ አለማጨስ እና የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.