Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ለአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለአለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ቀኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ76ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ65ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን÷የዘንድሮው የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን የሚከበረው “ከልብ ለሰብዓዊነ” በሚል መሪ ቃል ነው ተብሏል፡፡

መሪ ቃሉ በመላው አለም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የሚጎዱ ሰዎችን የሚታደጉ በጎ ፈቃደኞች እና ሠራተኞች በችግሮቹ መጠንና ስፋት የቆሙለትን ዓላማ ተረድተው የተረጂ ሰብዓዊ ፍጡራንን ተስፋ የሚያለመልም ሰብዓዊ አልግሎትን ከልብ ቅድሚያ የሚሰጡት መሆኑን ለማመልከት መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም ላለፉት 87 ዓመታት ሰብዓዊነትን በልባቸው ባነፁ በጎ ፈቃደኞችና ሠራተኞች እየተመራ ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ አንጋፋ ማኅበር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተባባሱ በመጡት ሰብዓዊ ቀውሶች በተለይም በግጭትና ድርቅ አደጋዎች ለጉዳት የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞችና ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መንቀሳቀሳቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የበጎ ፈቃደኞቹና ሠራተኞቹ ለሰብዓዊ አገልግሎት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ለሚያደርጉት ወደር የሌለው ሰብዓዊ መሰጠት ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡

ህብረተሰቡም በሰብዓዊ አገልግሎት የተሰማሩ የቀይ መስቀል ሠራተኞችና በጎፈቃደኞች ጎን በመቆም ለማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.