Fana: At a Speed of Life!

የሐረር ከተማን ለማልማትና በእቅድ ለመምራት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረር ከተማን ከማልማት እና በእቅድ ከመምራት አንፃር አመራሩ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ሐረር ከተማን ስትራቴጂክ በሆነ መልኩ ለመምራት ከተቋቋመው ክልላዊ ግብረ ሃይል ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ኦርዲን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ለሐረር ከተማ እድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች ለመፍታት በእቅድ መምራት ያስፈልጋል።

ሕዝቡን በንቃት በማሳተፍ ሐረር ከተማን በፕላንና በስትራቴጂ በመምራት ከተማውን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡

አመራሩ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባው ጠቁመው፥ በተለይም መሬትን በአግባቡ ለከተማው እድገት በመጠቀም ረገድ፣ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት እና የከተማውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የከተማዋን ፅዳትና ውበትን በማጎልበት፣ የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ እንዲሁም ገቢን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሕገ ወጥ ግንባታ እና የመሬት ወረራ ላይ የተጀመረውን የሕግ በላይነትን የማረጋገጥ ስራም በትኩረትና በቅንጅት መቀጠል እንዳለበት ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ የተመሰረቱ ሦስቱ የገጠር ከተሞች የኢኮኖሚ ማዕከል ሆነው ለወጣቱ የስራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የተቋቋመው ግብረ ሃይልም የሐረር ከተማን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት ከወዲሁ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.