Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በሙስና በተጠረጠሩ 1 ሺህ 322 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፏል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ 4 ሺህ 80 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል 1 ሺህ 322 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነትን ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሙስናን ለመከላከል  የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ የስራ ክንውኑን አስመልክቶ  በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚቴው በመግለጫው ÷ከሕዝቡ የቀረቡ 1 ሺህ 495 ጥቆማዎች በመመርመርና 642 የክስ መዝገቦችን በማደራጀት 1 ሺህ 322 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲተላለፍ ማድረጉን አንስቷል፡፡

በጥፋተኝነት ውሳኔውም ግለሰቦቹ ከ1 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ ከማድረግ ባለፈ በሕገ ወጥ መንገድ ከህዝብና ከመንግስት የተመዘበሩ ሀብቶች ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲሆን መደረጉም  ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም ውስጥ በጥሬ ገንዘብ 654 ሚሊየን ብር ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን÷ በባንክ ባለ የሂሳብ ደብተር ደግሞ ከ128 ሚሊየን ብር በላይ እንዲታገድ ተደርጓል ተብሏል፡፡

ከከተማ እና ከገጠር መሬት ምዝበራ ጋር ተያይዞ ኮሚቴው÷374 ሺህ 144 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት፣ 857 ነጥብ 97 ሄክታር የገጠር መሬት ተመላሽ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ከ846 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ላይ እገዳ እንደተጣለና ከዚህም ውስጥ ከ538 ሺህ ሄክታር መሬት በላዩ በኢንቨስትመንት ሰበብ የተወሰደ ነው ተብሏል።

ኮሚቴው 4 ህንፃዎችን፣ 33 ቪላና 8 ፎቅ ቤቶች ላይ እገዳ ማስጣሉን ጠቅሶ÷የሙስና ወንጀሎችን ለመግታት ፀረ ሙስና ኮሚቴው እያደረገ ያለውን የትግል ሂደት ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ከፀረ ሙስና ጋር ተያይዞ በ9909 ነፃ የስልክ መስመር ላይ በመደወል መረጃዎችን መስጠት እንደሚቻልም ገልጿል፡፡

ኮሚቴው በሁሉም ዞኖችና ከተሞች እንዲዋቀር በማድረግ ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ መሬት፣ ኢንቨስትመንት፣ ኮንስትራክሽን፣ የግዥ ሥርዓት፣ የታክስ፣ የትምህርት ዘርፎች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና የተጋላጭነት መጠናቸውን የሚቀንስ አሠራር እየዘረጋ መሆኑን የፀረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ከፍያለው ተፈራ ገልፀዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.