Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዙሪያ እየተወያየ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሀገረ-መንግሥት ግንባታና ብሔራዊ ማንነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እያካሄዱ ነው።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) የምክክር መድረኩ በተለይም በሀገረ-መንግሥት ግንባታና ብሔራዊ ማንነት ላይ በማተኮር ለአንድ ሳምንት ይካሄዳል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ያከበረ የጋራ ብሔራዊ ማንነት ግንባታን ከሀገረ-መንግሥት ግንባታ ጋር አስተሳስሮ ማስቀጠል የተረጋጋ ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥትና ብሔራዊ ማንነት ግንባታ ጋር ተያይዞ የአተገባበር ችግሮችን ለመፍታት በክርክር እና በሃሳብ የበላይነት የማሸነፍ ባህል መዳበር እንዳለበትም ገልጸዋል።

በመሆኑም በመድረኩ የሃሳብ ክርክሮችና ውይይቶች ተደርገው በኢትዮጵያ ምን ዓይነት የመንግሥት መዋቅር ያስፈልጋል? በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ ሃሳቦች ይነሳሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አጠቃላይ ሁኔታና ከብዝሃነት አንጻር ሊጠቅም በሚችለው የመንግሥት መዋቅር ዙሪያ የጋራ ምክር ቤቱ መምከሩ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ውይይት ለቀጣይ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች በጽንሰ-ሀሳብ ደረጃ መቀራረብ ለመፍጠርም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ከጉባዔው ጎን ለጎን በአርባ ምንጭ ከተማና ሌሎችም አካባቢዎች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.