Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ  የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኗ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ገለጹ፡፡

 

የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በፓኪስታን  በካራቺ ከተማ  መካሄድ  የጀመሯል፡፡

 

ፎረሙ  የሁለቱን ሃገራት ይበልጥ በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች  ላይ አትኩሮ በመካሄድ ላይ ነው።

 

በፎረሙ መክፈቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲኘሎማሲያዊ እና የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ባለፉት አምስት አመታት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

 

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ገልጸው÷ ዕድሉን የፓኪስታን ባለሃብቶች እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

 

የተሳለጠ የንግድ ልውውጥ በፓኪስታን እና በኢትዮጵያ መካከል እንዲኖር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም አምባሳደሩ አንስተዋል ።

 

የፓኪስታን ንግድ እና ልማት ባለስልጣን ሚኒስትር ዲኤታ ዙቤር ሞቲዋታ በበኩላቸው÷ ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ኢትዮጵያ ቁልፍ ሃገር መሆኗን ጠቁመው ሃገራቱ ያላቸውን እምቅ እና ተነፃፃሪ የቢዝነስ አቅም በመጠቀም የንግድ ልውውጣቸውን ማሳደግ አለባቸው ነብለዋል፡፡

 

በፎረሙ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቬስትመንት እና የቢዝነስ አማራጮች እና ምቹ ሁኔታዎችን ገለፃ እና ውይይት መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የመንግሰት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት  በፎረሙ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ  ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.