Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ28 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከመደበኛና ከአገልግሎት ገቢ ከ28 ነጥብ 28 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡

በቢሮው የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ አግማስ ጫኔ እንደገለጹት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመደበኛ ገቢ 24 ቢሊየን 528 ሚሊየን 312 ሺህ 194 ነጥብ 41 ብር ተሰብስቧል፡፡

በተጨማሪም ከአገልግሎት ገቢ 3 ቢሊየን 753 ሚሊየን 344 ሺህ 469 ነጥብ 44 ብር በድምሩ 28 ቢሊየን 281 ሚሊየን 656 ሺህ 662 ብር ቢሮው መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡

በ2015 በጀት ዓመት በአማራ ክልል 21 ሺህ 197 ከግብር ከፋዮች የቀረቡ የሂሳብ መዝገቦችን ለመመርመር ታቅዶ÷ በዘጠኝ ወራት 19 ሺህ 220 የሂሳብ መዝገቦችን መመርመር ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

ከእነዚህ የተመረመሩ የሂሳብ መዝገቦች 1 ቢሊየን 123 ሚሊየን 651 ሺህ 689 ብር ግብር ከፋዮች ካሳወቁት በላይ በልዩነት ማግኘት እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡

በአንድ ሂሳብ መዝገብ በአማካይ 75 ሺህ 155 ብር የተጭበረበረ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ጠቅሰው፥ ባለሙያዎች ቤት ለቤት በሚያደርጉት ክትትል 7 ሺህ 245 የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮችን መከታተል መቻላቸውንም አስረድተዋል።

ከደረሰኝ ጋር በተያያዘም ደረሰኝ የማይቆርጡ 1 ሺህ 509 ግብር ከፋዮች የ50 ሺህ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲቀጡ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በአስተዳደር እርምጃ ሊስተካከሉ ያልቻሉትን በወንጀል ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

በየሻምበል ምሕረት

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.