Fana: At a Speed of Life!

በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩት በእነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩት እነ ወንደሰን አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ በሶስት ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ14 ቀን ጊዜ ፈቀደ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፥ ፖሊስ በሽብር ወንጀል የጠረጠራቸውን ወንደሰን አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ በሶስት ተጠርጣሪዎች ላይ የተሰራ የምርመራ መዝገብን ተመልክቶ ነው ተጨማሪ ምርመራ መደረግ አለበት በማለት የ14 ቀን ጊዜ የፈቀደው።
ተጠርጣሪዎቹ፥ 1ኛ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ 2ኛ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር) እና 3ኛ ገነት አስማማው አያሌው ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የሰራቸውን የምርመራ ስራዎች ትናንት በነበረ ቀጠሮ ለችሎቱ አቅርቧል።
በዚህም ከስምንት ባንኮች ማስረጃ ማምጣቱን ፣የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ ማስነሳቱን እና በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 27/2 መሰረት የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን፣ የቴክኒክና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን በከፊል የማስመጣት ስራ ማከናወኑን ለችሎቱ ገልጿል።
የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ቀሪ የባንኮችና የተለያዩ ተቋማት ማስረጃዎችን ለማምጣት፣ በተፈጸመ የሁከትና አመፅ ማስነሳት ተግባር ላይ የደረሰውን የሰውና የንብረት መጠን የሚገልጹ ማስረጃዎችን ለማምጣት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፥ በፖሊስ ቀሪ ተብለው የቀረቡ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ዝርዝሮች ተጨማሪ ጊዜ ለማሰጠት የሚያስችሉ ምክንያቶች አይደሉም በማለት ተከራክሯል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ፥ በተሰጠን ጊዜ በርካታ ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ የሰራነውን የምርመራ ስራ ከመዝገቡ መመልከት ይችላል በማለት መልስ ሰጥቶ ነበር።
ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ይሸሽብኛል ሲል የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።
ተጠርጣሪዎቹ በመገናኛ ብዙኃን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታችን አልተጠበቀም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር።
አጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፥ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ አስፈላጊውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ተጨማሪ የምርመራ ስራ ማከናወን አስፈላጊነትን በማመን ለፖሊስ የ14 ቀን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ተጠርጣሪ መሰረት (ዶ/ር) ካጋጠማቸው የአስም የጤና ዕክል አኳያ ካሉበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ማቆያ ወደ ፌደራል ፖሊስ ማቆያ እንዲዛወሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት ተጥሶብናል ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በፌደራል ፖሊስ በኩል ተጣርቶ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ ታዟል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.