Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለረመዳን ጾም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለረመዳን ጾም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
 
“ታላቁ የረመዳን ወር የተቀደሰ የፆም፣ የፀሎትና የመንፈሳዊነት ወር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ በእስልምና ሃይማኖት የረመዳን ጾም ከአምስቱ የእስልምና መሰረቶች ውስጥ የሚመደብ መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
ይህንን ወር በቢሊየን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በመላም ዓለም በጾም፣ በመልካም ተግባር እና በፀሎት ያሳልፋሉም ብለዋል።
 
በረመዳን ወር ውስጥ ቁርዓን የተወረደበት የተባረከች ለሌሊት “የመወሰኛይቱ ሌሊት” ትባላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህች ሌሊት የሚተገበር መልካም ተግባርም ከ1 ሺህ ወራት መልካም ተግባራት የላቀ ምንዳ እንዳለው በቁርአን መጠቀሱንም አንስተዋል።
 
እንደ ወትሮው ቢሆን ይህ መልእክት የወራት ሁሉ አውራ ለሆነው የረመዳን ወር እንኳን አደረሳችሁ በሚል በጎ ምኞት ዙሪያ ብቻ ያጠነጥን ነበር ያሉ ሲሆን፥ የዚህ ዓመት ግን ዓለም በኮሮናቫይረስ በተጠቃችበትና ወረርሽኙን ለመከላከል አለመጨባበጥ፣ መራራቅና በቤት መወሰን ዋና የመከላከያ መንገድ ሆነው በሚተገበሩበት ጊዜ ነው የዋለው ብለዋል።
 
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል በመላው ዓለም መስጊዶችን ጨምሮ ቤተ እምነቶች ሁሉ መዘጋታቸውንም አስታውሰዋል።
 
“የእስልምና ሊቃውንት እንደሚያብራሩት አላህ በቸርነቱ ችግሩን አስወግዶ በነፃነት እንድናመልከው ያስችለን ዘንድ በየቤታችን ሆነን ለፈጣሪያችን መፀለይ እና መማፀን እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው በቀላሉ የሚተላለፉ የኮሮናቫይረስ አይነት ወረርሽኞች ሲከሰቱ መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ነብዩ መሃመድ ያስተማሩትን በዚህ ወቅት አበክረን ልንተገብረው ይገባልም ብለዋል።
 
ነብዩ መሃመድ የወርሽኞችን መስፋፋት ለመከላከል ካስተማሩት አንዱ የሰዎችን እንቅስቀሴዎች መገደብ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አስታውሰዋል።
 
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ሌላኛው የጥንቃቄ እርምጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በልዩ ማቆያ ስፍራ ለይቶ ማስቀመጥ ነው ያሉ ሲሆን፥ ይህ መከላከያም አቡዳውድ እንደዘገቡት “በተላላፊ በሽታ የተጠቁትን ከጤነኞች ለዩዋቸው” በማለት ነብዩ መሃመድ ካስተማሩት ትምህርት ጋር የተስማማ መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
የእስልምና እምነት ተከታዮች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመለየት ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተባባሪ እንደምትሆኑ ሙሉ እምነቴ ነውም ብለዋል።
 
“ንጽህና የእምነት ክፍል ነው ብለው ነብዩ መሃመድ እንዳስተማሩትም የቤተሰባችንንና የአካባቢያችንን ንፅህና በመጠበቅ ኮሮናቫይረስን በእምነትም በምግባርም እንከላከለው” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
 
“የረመዳን ወር አንዱ ትልቅ እሴት ዘካ እና ሰደቃ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ዘካ በታወቀ ተመን ከሀብት ላይ ለችግረኞች የሚሰጥ ሲሆን፥ ሰደቃ ግን በብዙ መልኩ ሊደረግ የሚችል መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው መቀዛቀዙን በማንሳትም፤ መንግስት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ሁለትንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቀውን ለማድረግ ግን ይህ የረመዳን ወር መልካም እድል መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ረመዳንን ለወቅታዊ ችግራችን መሸጋገሪያ እንጠቀምበት በማለት፤ የዚህ ዓመት ዘካ እና ሰደቃን ንግዳቸው ለተቀዛቀዘባቸው፣ የቤት ኪራይ የሚከፍሉትን ላጡ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል ለተቸገሩ፣ ልጆቻቸውን የሚያበሉ ላጡ ማዋል እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
 
“የኮሮና ወረርሽኝ ለብዙ ነገሮቻችን ተቃራኒ ሆኖ የመጣ ነው፤ መሰባሰብን፣ መቀራረብን፣ መጨባበጥን፣ ለወረርሽኙ መስፋፈያ እየተጠቀመበት ነው፤ በዚህ ምክንያት ከእንደዚህ ነባር ልማዶቻችን ለጊዜው እንዲንለይ ተገደናል፤ ስለዚህ የዘንድሮን ረመዳን በየቤታችን ሆነን በቤተሰብ ደረጃ ብቻ አካላዊ ርቀታችን ጠብቀን እንዲናከብረው ተገደናል፤ ይህንን የችግር ወቅት በፈጣሪ እርዳታና በጋራ ጥረታችን አልፈን ረመዳንን እንደ ጥንቱ እሴቶቻችን ጠብቀን እንደምናከብረው ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።
 
በዚህ የተቀደሰ የረመዳን ወር ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ የነባር እምነቶች ተከታዮችና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚህ ወረርሽኝ ላይ በጋራ እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.