Fana: At a Speed of Life!

የአጥንት መሳሳት መንስዔ እና የመከላከያ ዘዴዎች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤናማ እና ጠንካራ አጥንት ለሰውነታችን የተለያዩ ክፍሎች ከለላ በመሆን ከማገልገል ባሻገር ለጡንቻዎቻችን ጠንካራ መሠረት ሆነው በዕድሜያችን ማምሻ የተስተካከለ እና ያልጎበጠ አቋም እንዲኖረን ያስችሉናል፡፡

ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የአጥንት መሳሳት በደካማ የአመጋገብ ሥርዓት ፣ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ባለመሥራት እና በምንከተላቸውን ጤናማ ያልሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎች በጉልኅ ይስተዋላል፡፡

ጤናማ እና ጠንካራ አጥንት እንዲኖረን በልጅነታችን እና በጉርምስናችን ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች ልብ በማለት ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡

ወደ ጉልምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ ገብተንም ቢሆን የአጥንትን ጤንነት እና ጥንካሬ መጠበቅ እንደሚቻል በጤና እና በአኗኗር ዘይቤ ላይ መረጃ የሚያጋራው “ማዮ ክሊኒክ” ፅፏል፡፡

ፅሑፉ እንደሚያስረዳው በተለምዶ “ሠፊ አጥንት” ለሚባለው ዓይነት ጠንካራ እና ጤናማ የሰውነት አጥንቶች ግንባታ ፣ ወይም በሌላ አገላለፅ የተስተካከለ / “ቀጥ ላለ” ተክለ-ሰውነት መሠረት መጣል የሚጀመረው እና የሚገባደደው ከልጅነት እስከ 30 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ነው፡፡

ከ30 ዓመት በኋላ የሰውነት አጥንቶች ቅርፅ እየተለወጡ እና እየሳሱ ይሄዳሉ፡፡

ሀ. የሰውነታችን አጥንቶች በምን ምክንያት ይሳሳሉ ?

በምንመገበው ምግብ ውስጥ የሚገኘው የካልሲየም መጠን ማነስ ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለመሥራት ፣ ሲጋራ ማጨስ ፣ አዘውትሮ አልኮል መጠጣት ፣ አነስተኛ የሰውነት ክብደት (ቀጭን መሆን) ፣ የዕድሜ መግፋት ፣ ዘር (ለምሳሌ ነጮች እና የእስያ ዝርያ ያላቸው ሰዎች) ፣ ከፍተኛ የታይሮይድ ሆርሞን መጠን በሰውነት ውስጥ መኖር ፣ የሴቶች የኤስትሮጂን ሆርሞን መቀነስ እና ማረጥ (መውለድ ማቆም) እንዲሁም በወንዶች ላይ የቴስቴስትሮን ሆርሞን መጠን መቀነስ ለአጥንት መሳሳት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተፈጥሮ ከወንደች ይልቅ ሴቶች ለአጥንት መሳሳት እንደሚዳረጉም ተመልክቷል፡፡

የ“ኮርቲኮስቴሮይድ” መድሐኒቶችን ለረጅም ጊዜ መጠቀምም ለአጥንት መሳሳት ምክንያት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለ. የሰውነታችን አጥንቶች ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ ምን ማድረግ አለብን ?

1. በአመጋገብዎ ወተት እና የወተት ተዋፅዖዎችን ፣ ዓሳ ፣ አኩሪአተር ፣ አልመንድ ፣ ብሮኮሊ ማዘውተር ፤

የተጠቀሱትን የምግብ ዓይነቶች በበቂ መጠን ለማግኘት ከተቸገሩ ሐኪም በማማከር የካልሲየም እንክብል ወይም ሌሎች ምትክ መድሐኒቶችን / ንጥረ-ነገሮችን ሊያገኙ ይችላሉ።

2. በቂ የፀሐይ ሙቀት እና ሌሎች “ቫይታሚን ዲ” ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን ዕንክብሎች /ምንጮች ሐኪም በማማከር ይውሰዱ ፤

3. አዘውትሮ በእግር መሄድን ጨምሮ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን መሥራት ፤

4. ከማጨስ ይቆጠቡ ፤

5. በቀን የሚጠጡትን የቡና መጠን ይቀንሱ ፤

6. የአልኮል መጠጦችን አያዘውትሩ ፤

በተለይ ዕድሜዎ እየጨመረ ሲሄድ እና የመገጣጠሚያ ሕመምን ጨምሮ ድካም ሲሰማዎ ለአጥንትዎ የሚበጁ የካልሲየም ንጥረ-ነገሮችን ሐኪም ሊያዝልዎ ስለሚችል በጉዳዩ ላይ የጤና ተቋማትን ማማከር እና የሕክምና ክትትል ማድረግ አይርሱ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.