Fana: At a Speed of Life!

ከንጹሐን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ የጋምቤላ ክልል የቀድሞ የፖሊስ እና የልዩ ኃይል አዛዦችን ጨምሮ በ15 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንጹሐን ዜጎች ግድያ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩ የጋምቤላ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል አዛዦችን ጨምሮ በ15 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ክሱ የተመሰረተው ተጠርጣሪዎች የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ ፣ ም/ኮሚሽነር ቱት ኮር ፣ የክልሉ የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡጀዲ ባሬን እና የተለያዩ የፀጥታ አባላትን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ተጠርጣሪዎች ላይ ናቸው።

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ (ጋነግ) በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ በቀበሌ 3 በኩል በመግባት በፌደራል ፖሊስ ካምፕ እና በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም በሌሎች ፀጥታ አካላት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በተከፈተበት ወቅት በፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት እንዲመለስ መደረጉ ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹም በከተማው የሚኖሩ ንጹሀን ዜጎችን በማንነት በመለየት፣ የሸኔ የሽብር ቡድን ደጋፊ ናችሁ መረጃ ሰጥታችኋል ” በሚል ምክንያት ማንነታቸው የተለዩ 35 ሰዎች እና ማንነታቸው ያልተለዩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ትዕዛዝ በመስጠትና በመግደል ጭምር ተሳትፎ አላቸው ተብለው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር ይታወሳል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ መርማሪ በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራ በሰነድና በሰው ማስረጃ አጠናክሮ በማጠናቀቅ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ተከትሎ የፍትህ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ መሰረት ዛሬ በተከሳሾቹ ላይ በመደበኛ ችሎት ክስ መስርቶባቸዋል።

በጦርነት ጊዜ ንጹሐን ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን የጄኔቫ ቃል ስምምነት የፕሮቶኮል ድንጋጌን በመለተላለፍ እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ1/ለ ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 270 /ሀ ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።

በዚህ መልኩ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተ ቢሆንም የችሎቱ አንደኛው ዳኛ በጽህፈት ቤት በመገኘት የቀረበውን ክስ በተሟላ ዳኛ ለመመልከት በይደር ለነገ ቀጥረዋል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.