Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ ነው – የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብ ነክ የዕለት እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ በሺር አረብ እንደገለጹት÷በክልሉ ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ኤረር፣ ኖጎብና ጀረር ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ አጋጥሟል።

በክልሉ ባለፉት ሣምንታት ጀምሮ በ38 ወረዳዎች ውስጥ የጣለው ከባድ ዝናብና በኦሮሚያ ክልል ባሌና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች ከፍተኛ ቦታዎች ላይ እየጣለ ባለው ዝናብ የዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ወይብና ጀረር ወንዞች ከመጠን በላይ ሞልተው በመፍሰሳቸው በወንዞቹ አቅራቢያ የሚገኙ 211 መንደሮች በጎርፍ ተጎድተዋል ብለዋል።

በመንደሮቹ በደረሰው የጎርፍ አደጋ 30 ሺህ 249 አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በሄሊኮፕተርና በጀልባዎች በመታገዝ ተጎጂዎች የጎርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ለቀው ደረቃማ ወደ ሆኑ ስፍራዎች እንዲሰባሰቡ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

እስካሁን ለ10 ሺህ 512 ወገኖች ከ3 ሺህ 40 ኩንታል በላይ ሩዝ፣ የዳቦ ዱቄትና አልሚ ምግብ እንዲሁም 438 ሊትር የምግብ ዘይት ቀርቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጎርፍ አደጋው 20 ሺህ የሚጠጉ የቤት እንስሳት መሞታቸውን፣ 45 ሺህ ሄክታር ያህል መሬት ላይ የነበረ የሰብል ቡቃያ መውደሙንም አቶ በሺር ተናግረዋል።

እንዲሁም 108 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና ኬላዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው ÷ 317 የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በጎርፍ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሶማሌና አጎራባች ክልሎች ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዘሪሁን ኃይለማርያም እንደገለጹት÷ በአብዛኛው የክልሉና በምስራቁና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ እየጣለ ነው።

በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ በያዝነው ግንቦት ወርም እንደሚቀጥል የሜቲዎሮሎጂ የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።

ሕዝቡ ከውሃ አካላትና ከወንዞች አካባቢዎች በመራቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም  አስጠንቅቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.