Fana: At a Speed of Life!

አንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።

ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ባደረባት ህመም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በህክምና ስትረዳ ቆይታ ህይወቷ ማለፉን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከቤተሰቦቿ ተረድቷል።

ሂሩት በቀለ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት ድምፃዊያን መካከል አንዷ እና ተወዳጇ ናት።

ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿም በህዝብ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እንዲሁም ለበርካታ ሴት ድምፃዊያንም መነሻ የሆኑም ናቸው።

ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መካከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” አንዱ ነው።

ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የትያትር ክፍል ውስጥ ለ35 ዓመት አገልግላለች።

በ35 ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ከ38 በላይ ሙዚቃዎች በሸክላ የታተሙት ናቸው።

በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ አልበሞችን አበርክታለች።
ድምጻዊት ሂሩት የሰባት ልጆች እናትም ነበረች።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድምፃዊቷ እረፍት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ፥ ለዘመዶቿ እና አድናቂዎቿ መፅናናትን ይመኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.