Fana: At a Speed of Life!

6ኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የገቢ ንግድ ትውውቅ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የገቢ ንግድ ትውውቅ ጉባኤ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አስመጪና ላኪዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ማሳደግ እና ማስተዋወቅ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ በሚመክረው ጉባኤ፥ ከሁለቱም ሀገራት የተወከሉ የንግድ ምክር ቤት አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የልምድ ልውውጥ እያደርጉበታል ተብሏል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን እንዳሉት ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በብዙ መስኮች እየተጠናከረ መጥቷል።

ሃገራቱ በተለይም በንግድ እና በኢንቨስትመንት መስኮች ትብብራቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፥ በፈረንጆቹ 2022 የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጣቸው 2 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና የንግድ አጋሮች መካከል በቀዳሚነት ትቀመጣለች ያሉት አምባሳደሩ መንግስታቸው የሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ጠንካራ ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ዳኛቸው አትንኩት በበኩላቸው የቻይና እና ኢትዮጵያ የንግድ እና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ከፍተኛ እድገት እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዓመት ህዳር ወር ላይ ኢትዮጵያውያን አምራቾች እና ላኪዎች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በቻይና ሻንጋይ ከተማ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ፍሰት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.