Fana: At a Speed of Life!

ቴድሮስ አስፋውና ዳዊት በጋሻው በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ፖሊስ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍድር ቤቱ ቴድሮስ አስፋውና ዳዊት በጋሻው በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ፖሊስ የሚያካሂደውን ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ ተገቢ የምርመራ ስራ አከናውኗል በማለት የምርመራ ስራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ነው ተጨማሪ 14 ቀን ጊዜ የፈቀደው።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከዚህ በፊት የተሰሩ የምርመራ ስራዎችንና የተጠርጣሪ የመከራከሪያ ነጥቦችን ተመልክቷል።

በዚህም ከባንኮች ማስረጃ እንዲመጣለት መጠየቁን ፣ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 27/2 መሰረት የተከሳሽነት ቃላቸውን መቀበሉን እዲሁም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ለችሎቱ ገልጿል።

የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ የባንኮችና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃዎችን ለማምጣት፣ ተፈጸመ በተባለው የሁከትና አመፅ ማስነሳት ተግባር ላይ የደረሰውን የሰውና የንብረት ጉዳት መጠን የሚገልጹ ማስረጃዎችን ለማምጣት እና ቀሪ ተጠርጣሪ ግብረ አበሮችን ለመያዝ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ጠቅሷል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው÷ ለ29 ቀናት ተጠርጣሪዎች በስር በቆዩባቸው ጊዜያት መሰራት የነበረባቸው የምርመራ ስራዎች ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ መጠየቂያ ምክንያትነት ሊቀርቡ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

በፖሊስ ቀሪ የምስክር ቃል ለመቀበል ተብሎ የተገፀውን በሚመለከት ስንት ምስክር ተቀበሉ ስንትስ ቀረ የሚለውን እና ቀሪ ግብረ አበሮች የተባሉት እነማን እንደሆኑ ባልተገለፀበት ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ ሊሆን አይገባም ሲሉ መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸውም ጠበቆቹ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ በተሰጠው ጊዜ በርካታ ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ ÷ዝርዝር ነጥቦች ለፍርድ ቤቱ በቀረበው መዝገብ ውስጥ መካተታቸውን በመጥቀስ መልስ ሰጥቷል።

ምስክሮችንና ተጠርጣሪ ግብረአበሮችን በሚመለከት ማን እና የት የሚለውን መግለፅ ግን ለምርመራ ስራው እንቅፋት እንደሚሆን የገለፀው ፓሊስ÷ ቀሪ ምስክር ቃል በመቀበልና ተጨማሪ ተጠርጣሪ ግብረ አበሮችን በክትትል የመያዝ ስራ እንደሚሰራ ገልጿል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ወደ ውጭ ሊሸሹና የምርመራ ስራውንም ሊያደናቅፉ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

ተጠርጣሪዎቹ ቴድሮስ አስፋውና ዳዊት በጋሻው በሙያችን ከመስራት ውጪ በሽብር ወንጀል የሚያስጠረጥር ማስረጃ ካለ ተሳትፏችን ይገለጽልን ሲሉ ባቀረቡት ጥያቄ መነሻ ተሳትፏቸውን ተለይቶ እንዲያብራራ መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ የማጣሪያ ጥያቄ ለፖሊስ ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪ ዳዊት በሙያ ስራው ሳይሆን በሽብር ወንጀል ተግባር ያደረገውን የግንኙነት የቴክኒክ ማስረጃ በመገኘቱ ነው በሽብር ወንጀል የጠረጠርነው ሲል ምላሽ የሰጠ ሲሆን÷ቴድሮስን በሚመለከት የጥርጣሬ መነሻው በምርመራ መዝገቡ መገለፁን ፖሊስ በምላሹ አንስቷል።

በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ፎቷችንን በመጠቀም ዘገባዎች ተሰርተውብናል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

አጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ በተገቢው መንገድ አልሰራም የሚለውን የጠበቆችን መከራከሪያ ነጥብ በሲዲ የተደገፉ የምርመራ ማስረጃዎች በመቅረባቸውና በተሰጠው ጊዜ ተገቢ ምርመራ አድርጓል በማለት መከራከሪያውን እንዳልተቀበለው የችሎቱ ዳኛ አብራርተዋል።

የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግም ፓሊስ ተጨማሪ የምርመራ ማጠናቀቂያ ስራ አከናውኖ እንዲቀርብ በማሳሰብ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ በችሎቱ ምንም አይነት ትዕዛዝ አልተሰጠም።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.