Fana: At a Speed of Life!

በመጪው 5 ዓመታት የስኳር ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው አምስት ዓመታት የስኳር ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ እንደገለጹት÷ የሀገር ውስጥ የስኳር ምርትና አቅርቦት ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።

ይህንንም ተከትሎ የስኳር ምርት አቅርቦትንና ፍላጎትን ለማጣጣም በማሰብም መጋቢት 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደገና መቋቋሙን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ ግሩፑ እንደገና ሲቋቋም የሀገር ውስጥ የስኳር ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ማሟላት የሚያስችለውን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በዚህም ለሸንኮራ አገዳ ምርት መቀነስና ለማምረቻ ወጪ መናር ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫን ተመላክቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች የመስኖ መሰረተ ልማት ለማስፋትም ትኩረት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

በዚህም ከ2020 ዓ.ም ጀምሮ የስኳር ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ በመተካት ከውጪ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ፋብሪካዎች ራሳቸው ከሚያለሙት የሸንኮራ አገዳ ምርት በተጨማሪ በአከባቢያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮችና ማኅበራት የሚያለሙትን የሸንኮራ አገዳ በመግዛት ለግብዓትነት የመጠቀም ልምድ መኖሩንም ገልጸዋል።

በመጪው አምስት ዓመታት የስኳር ምርትን አሁን ካለበት 3 ሚሊየን 640 ሺህ ኩንታል ወደ 13 ሚሊየን ኩንታል ለማሳደግ ዕቅድ መያዙንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአገሪቱ አሁን ላይ ከሰም፣ ወንጂ ሸዋ፣ አርጆ ደዴሳ፣ ኩራዝ 02፣ ኩራዝ 03፣ በለስ ቁጥር 1፣ መተሐራና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች በሥራ ላይ አንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.