Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የታክስ ተገዥነት ንቅናቄና የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መስጫ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እና ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ግብር ከፋዮች ተገኝተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ መንግስት ገቢ የመስብስብ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የክልሉ ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት ከ38 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን የጠቆሙ ሲሆን÷ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምን ጨምሮ ሁሉም ወደ ገንዘብ መቀየር የሚችሉ የአገር ትልቅ ሀብቶች ናቸው ብለዋል።

ትልቅ የገቢ አቅም የሚሆን ሀብት ቢኖርም በየደረጃው ያሉ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት አገሪቷ የሚያስፈልጋትን ገቢ በበቂ ሁኔታ እየሰበሰቡ አይደለም ነው ያሉት።

በተለይም በደረሰኝ ገቢ የመሰብሰብ ችግር፣ ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ ንግድ ትልቅ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገቢ አሰባሰብ አቅም ማደግ መቻሉ ሁሉም በጋራ ተባብሮ ከሰራ ትልቅ ለውጥ የሚመጣ መሆኑን ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኦሮሚያ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 54 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተመላክቷል።

በመድረኩ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የታክስ ሕግ ተገዢነት ንቅናቄ ይፋ መደረጉንም አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.