Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል ከበልግ እርሻ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል – ቢሮው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል በበልግ ወቅት ከሚለሙት ዋና ዋና ሰብሎችና ሥራ ሥር ተክሎች ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ÷ በክልሉ ያለውን የበልግ እርሻ አቅም ተጠቅሞ ስኬታማ ለማድረግ የአመራሩ፣ የፈጻሚውንና የአርሶ አደሩን በተደራጀና በማቀናጀት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል ፡፡

በዚህም ከ105 ሺህ 117 ሄክታር በላይ መሬት በቆሎ፣ ቦሎቄና ድንችን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ሥር ተክሎች ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 88 በመቶው ያህሉ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ካለው የዝናብና መልካም አየር ጸባይ የተነሳ የምርት አያያዙ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ሃላፊው÷ በክልሉ የበልግ እርሻ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የበልግ እርሻ ስራ ግብርናን በሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዝ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሩ ክትትል በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የጋራ የሆነ የግብዓት አጠቃቀም፣እንክብካቤ፣ የምርት አሰባሰብና የገበያ ትስስር የሚፈጥር የግብርና ልማት በማካሄድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የአረም፣ በሽታና የተባይ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው÷ እየጣለ ያለው ዝናብ አሉታዊ ተፅእኖ በሚፈጥርባቸው አካባቢዎችም ውሃ የማፋሰስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎችም የማሳ ውስጥ የውሃ እቀባ ሥራ በማከናወን የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን÷ በቆሎ ለሚዘሩት ወረዳዎች ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በበልግ እርሻ 333 ሺህ 468 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን÷ በዋና ዋና ሰብሎች በቆሎና ቦሎቄ፣ ከሥራ ሥር ድንችና ስኳር ድንችን ጨምሮ ሌሎችም መልማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.