Fana: At a Speed of Life!

የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአዲስ መልክ ማደራጀት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማጠናከር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

አሁን በሥራ ላይ ያለው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 ላለፉት ሃያ ዓመታት በሥራ ላይ መቆየቱ ይታወቃል።

የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የገለጸው።

ሚኒስቴሩ ያዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የንግድ ሥራ በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በ2013 የተሻሻለው የንግድ ሕግ በርካታ ወቅቱን የጠበቀ ማሻሻያዎች እንደተደረጉበት ገልጸው አደረጃጀቶችም ከዚሁ አዋጅ ጋር መጣጣም እንዳለባቸው ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ረቂቅ አዋጁን ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረጉ ተከታታይ ውይይቶች በማዳበር በተያዘው እቅድ መሰረት የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን በዚህ ዓመት ለማጸደቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የላይሰንሲንግና ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጅራታ ነመራ በበኩላቸው አዋጁ ከስያሜ ጀምሮ በርካታ አዲስ ነገሮችን ይዞ መቷል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

የአዋጁ ማሻሻያ ያስፈለገው የተደራጀ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.